የአማራ ወጣቶች ማህበርን እናስተዋውቅዎ !
በአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ለዉጥ እና ዉጤት እንዲመጣ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና በአግባቡ መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ ታዲያ ይህ የሚፈለገዉ ዉጤት እንዲመዘገብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካለባቸዉ የማህበረሰብ ክፍል መካከል ወጣቱ ትዉልድ ዋነኛዉና ጉልህ ሚና ያለበት ነዉ፡፡ወጣቶች እንደሌላዉ የማህበረሰብ ክፍል በንቃት እና በትጋት በልዩ ልዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ የለዉጥ ዋነኛ ሞተር መሆን ይጠበቅብናል፡፡
ወጣትነት የትኩስ ሃይል ባለቤትነት ነዉ ፤ ወጣትነት የለዉጥና የአዲስ ነገር ትግበራ ጉጉት ገዝፎ የሚታይበት ወቅት ነዉ፡፡ ወጣትነት የነገ ሀገር አምሳያ የሚፈጠርበት ቅርፀ- ተምሳሌት ነዉ፡፡በመሆኑም ይህንን ሃይል እና ተፈጥሮ በአግባቡ መምራትና ወደሚፈለገዉ መስመር መምራት ለነገ የማይባል ጉዳይ ነዉ፡፡ ታዲያ ይህንን ሃይል በአግባቡ ለመጠቀም ደግሞ በአንድ እና በሌሎች መዋቅራዊ ቅርፅ ባላቸዉ አደረጃጀቶች ማሳተፍ እና የአደረጃጀቶቹም ባለቤት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በተለይም ወጣቶች ህገ መንግስታዊ ስርአቱ ያጎናፀፋቸዉን እድሎች ተጠቅመዉ ያሉባቸዉን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በመቅረፍ ተጠቃሚነታቸዉን ለማረጋገጥ እንዲሁም በሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በንቃት ለመሳተፍ እንዲችሉ የራሳቸዉን ማህበር / አደረጃጀት መመስረት ተገቢ ነዉ፡፡
እነዚህ አደረጃጀቶች ደግሞ ወጣቶች ዲሞክራሲያዊ ፣ሰብአዊ ፣ ፖለቲካዊ እና መሰል መብቶቻቸዉን የሚያዳብሩባቸዉ ፤ የሚያስፈልጋቸዉን ልምድ እና ተሞክሮ የሚያገኙበት ፤ ጥቅማቸዉንም የሚያረጋግጡበት በጥቅሉ ስብእናቸዉን እና አቅማቸዉን የሚገነቡባቸዉ ናቸዉ ፡፡
የአማራ ወጣቶች ማህበርም ከላይ የተገለፁትን ቁልፍ ሃሳቦች መነሻ በማድረግ የወጣቶችን ሁለንተና ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም በንቃት ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማስቻል በጥቂት ወጣቶች ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ፤ በተለያዩ አጋር አካለት ድጋፍ በ 1995 ዓ.ም ተመስርቷል፡፡
ማህበሩ ለማናቸውም የፖለቲካም ሆነ የሀይማኖት ተቋማትና ድርጅቶች የማይወግን ፤ ነፃ ማህበር ሆኖ በሚመለከታቸዉ አካላት እዉቅናና ፈቃድ መሰረት በአዋጅ ቁጥር 194 መሰረት ተቋቁሟል፡፡
ከ1995 ዓ.ም ከተመሰረተ ጀምሮ በፍትሃ ብሔር ህግ አንቀጽ 404 እና ተከታዮቹ መሰረት ተመዝግቦ ህጋዊ ሰውነት የነበረውና አሁንም የበጐ አድራጐትና ድርጅቶችን ለመመዝገብ እና ለማስተዳደር ባወጣው አዋጅ ቁጥር 194 አንቀጽ 63/1/ መሰረት እውቅና ያለዉ ማህበር ነዉ ፡፡
ይህ በ1995 ዓ.ም የተመሰረተዉና 22 አመታትን ያስቆጠረዉ የአማራ ወጣቶች ማህበር አሁን ላይ ከ 1.9 ሚሊየን በላይ አባላት እና በሁሉም የክልላችን ዞኖች ፣ በከተማ አስተዳደሮች ፣ በወረዳዎች ፣ በቀበሌዎች እና በአዲስ አበባ የማህበሩ ቅርንጫፎች አሉት፡፡
—–
ማህበሩ የተመሰረተባቸዉ ዋናዋና አላማዎችም የሚከተሉት ናቸዉ፡፡
1-/የወጣቶች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት ማድረግ፣
2/ ወጣቱ ትውልድ ህብረተሰቡ ከኋላ ቀርና ከጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲላቀቅ ተገቢውን ሚና እንዲጫወት ማድረግ፣
3/ ወጣቶች ለክልሉ ዘላቂ ልማት ንቁ ተሳታፊ በመሆን የህብረተሰቡና የራሳቸዉ የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል ጥረት ማድረግ፣
4/ የወጣቶች የስራ አጥነት ቁጥር ለመቀነስ የስራ ፈጠራ ተቋማቶችና ኢንተርኘራይዞች እንዲቋቋሙና እንዲስፋፉ ማድረግ፣
5/ በክልላችንም ሆነ ከክልላችን ውጭ ለሚኖሩ የአማራ ወጣቶች የማህበሩን ሁለንተናዊ ገፅታ እንዲያውቁት በማድረግ በፍላጐታቸው ወደ ማህበሩ እንዲቀላቀሉ ማድረግ፣
6 / በክልላችን የመልካም አስተዳደር እንዲሰፍን እና የዲሞክራሲ ባህል እንዲጐለብት ጥረት ማድረግ፣
7 / ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ መንግስት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና ፓኬጆች ወጣቶችን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን መከታተልና ማገዝ፣
8 / ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን እንዲያከናውኑና በኘሮግራሞቻቸው በኘሮጀክቶችና በእቅዳቸው ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን አካተው ተግባራዊ እንዲያደርጉ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ በትብብር መስራት፣
9 / መንግስት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጅዎች ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን መከታተልና፣ ክፍተቶች ሲኖሩ ክፍተቶቹ እንዲሞሉ ለሚመለከታቸው አካላት ግብአት መስጠት፡፡
10/ ማህበሩ የራሱን የውስጥ ገቢ ለማሳደግ የሚያስችሉ የገቢ ማስገኛ ስርዓት በመዘርጋት ወጣቱንና ማህበሩን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ ዋና ዋና ዎቹ ናቸዉ፡፡
በቀጣይ ስለማህበሩ አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴና ዉጤት ፣ እንዲሁም ወቅታዊና ተቋማዊ ገፅታን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃዎችን እናደርሳለን ፡፡
#እኔ_ስልጡን_ወጣት_ነኝ ! #_እንደ_ወጣትነቴ_በምክንያታዊነት_አምናለሁ##_አስተዉላለሁ_አመዛዝናለሁ_እወስናለሁ
#_የአማራ_ወጣቶች_ማህበር_ዋና_ፅ/ቤት_ባህርዳር
#_Amhara_Youth_Association_Head_Office_Bahirdar
#_Amhara_Youth_Association_Offical_Face_book_Page
